+251-58-178-0033prcd@dmu.edu.et
logo
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

Debre Markos University

Grow wiser at the water tower
👥 Staff ProfileLogin

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአንጋፋው ደራሲና ዲፕሎማት ሐዲስ ዓለማየሁን የህይወት እና የስራ ታሪክ የሚዘክር  መጽሐፍ አስመረቀ

Nov 18, 2026
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በባህል፣ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የታላላቅ ደራሲያንን የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎችና ታሪኮች በመሰነድ ለአንባቢያን የማድረስ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም መሠረት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጽሕፈት ቤት ያዘጋጀውን የአንጋፋው ደራሲና ዲፕሎማት ሐዲስ ዓለማየሁን የህይወት እና የስራ ታሪክ የሚዘክር  መጽሐፍ  ጥቅምት 28 ቀን 2019 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው የሐዲስ ዓለማየሁ የጉባኤ አዳራሽ በይፋ አስመረቋል። የ”ሃዲስ ትዉስታ” በሚል ርዕስ ለህትመት የበቃዉ መጽሃፍ ክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ከዓመታት በፊት ከፕሮፌሰር ዓለም ሃብቱ ጋር ያደረጉትን የ53 ሰዓት ቃለምልልስ ወደ ጽሁፍ በመቀየር የተሰናዳ ሲሆን በዝግጅት ሂደቱ በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበት መሆኑ ታዉቋል፡፡ በመጽሐፉ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት  የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት መልካሙ በዛብህ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የዕለቱ መድረክ የመጽሐፍ ምረቃ ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲው ለባህል፣ ለቋንቋና ለሥነ-ጽሑፍ ጥናትና ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተግባራዊ ማሳያ ነው። መጽሐፉም የቀደመውን ጥረት በማስቀጠል የታሪክ ሰነዶችን ለማስጠበቅ፣ የሥነ-ጽሑፍ ውርስን ለማስፋት እና ለአዲሱ ትውልድ የማንበብ፣ የማሰብና የመመራመር ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳይህ ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው በፕግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ከዩኒቨርሲቲው ዋና ዋና ተልዕኮዎች አንዱ አካባቢያዊ ጸጋዎችን፣ ሀገር በቀል ዕውቀትን፣ ባህልን እና ዘመን ተሻጋሪ የሥነ-ጽሑፍ ሀብቶችን መጠበቅና ማጎልበት መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ የተመረቀው “የሐዲስ ትውስታ” መጽሐፍ ክቡር ሐዲስ ዓለማየሁ ከፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ ጋር ያደረጉትን የ53 ሰዓታት ጥልቅ ቃለ መጠይቅ ዩኒቨርሲቲው በአደራ ተቀብሎ ለታሪክ፣ ለምርምርና ለሥነ-ጽሑፍ መሠረት በሚጥል መልኩ አዘጋጅቶ ለሕትመት ማብቃቱ እጅግ የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። በዕለቱ ታዋቂው ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ቁልፍ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን፤ ሐዲስ ዓለማየሁ ሀገር በቀል ዕውቀትን የቀሰሙ፣ በሙያቸውና በሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ለሀገራቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ የጥበብ ሰው መሆናቸውን ገልጸዋል። በመርሐግብሩ በመጽሃፉ ዙሪያ ያጠነጠኑ ሁለት መወያያ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ይሄይስ አረጉ (ዶ/ር) የደራሲ ዲፕሎማትና ሐዲስ ዓለማየሁ ለሀገር ያበረከቱትን ስራዎችና አበርክቶዎች በማስመልከት ጥልቅና ሰፊ ትንተና በዝርዝር ቀርቧል። ከዶ/ር ይሄይስ በተጨማሪም አቶ ደረጀ መለሰ  ከሐዲስ ዓለማየሁ የታሪክ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ አበርክቶዎች ትውልዱ ምን ይማራል የሚል ይዘት ያለዉ  ሰፊ ዳሰሳና ምልከታ አቅርበዋል። የቀረቡትን የመጽሃፍ ዳሰሳዎች መሰረት በማድረግም በፕግራሙ ታዳሚዎች ዉይይት የተደረገ ሲሆን ተወያዮች ዩኒቨርስቲዉ ይን መጽሃፍ በማሳተም ትልቅ ታሪካዊ ተግባር መፈጸሙን አድንቀዋል፡፡

Our Partners